Saturday, April 25, 2015

ለኢትዮጵያውያን ወገኖቹ የቆመ ምርጥ ኤምባሲ

ሰው ከባንዲራው ሌላ ወዴት ይጠለላል?
ለኢትዮጵያውያን ወገኖቹ የቆመ ምርጥ ኤምባሲ
በፀሐይ በየነ

የመን በጦርነት መታመስ ከጀመረች ሳምንታት ነጉደዋል፡፡ የአለም ሚድያዎች ስለጦርነቱ ለመዘገብ አይናቸውንና ካሜራቸውን ወደእሷው አዙረዋል፡፡ የትኛውንም የቴሌቭዥን ጣቢያ ቢከፍቱ የየመንን ስም የማያነሳ ጣቢያ አያገኙም በስቅታ ሞታለች፡፡ አብዛኛዎቹ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ከየመን በቀር ሌላው አለም የጠፋ እስኪመስል ድረስ ርስት አድርገው ከዜና መጀመሪያቸው እስከ ፍፃሜው ድረስ በየመን ያለውን ችግር የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞችን ትንተና እያሰጡ በሷው ጀምረው በሷው ይጨርሳሉ፡፡
የአለም ባለስልጣናት በሚያምር አዳራሽ፣በተዋበ ጠረጴዛ፣ ድሎት በሚሰጥ ወንበር ፣ በሱፍ በከረባት አምረው በጦርነቱ ዙሪያ ሲመክሩ ይውላሉ፡፡ ምንም ግን ለየመን ህዝብ ያመጡት ፋይዳ የለም፡፡ በየቀኑ ብዙዎች ይሞታሉ ብዙዎች ይቆስላሉ በተለይ ኤደንና ትዕዝ በሚባሉ የየመን ከተሞች፡፡
ሰነዓ ከተማ በጦርነቱ ምክንያት መብራት ስለተቋረጠ ከተማዋን የብርሃን ናፍቆት ግድል አድርጓታል፡፡ መንገዶች ተመቱ በሚል ሰበብ ነዳጅ በመጥፋቱ መኪናዎች እና ሞተሮች በነዳጅ ጥም መንቀሳቀስ ስላልቻሉ በየመንገዱ በመቆማቸው መንገድ ሁሉ የመኪና መሸጫ እስኪመስል ድረስ በብዛት ተኮልኩለው ይታያሉ፡፡
በጦርነቱ ፍራቻ ከተማዋን በመልቀቅ ወደ ገጠር ህዝቡ ስለሸሸ በፊት በግፍያ ትከሻዎን የሚያወልቀው የህዝብ ብዛት ጠፍቶ ሰው ለማግኘት አይኖት ይንከራተታል፡፡ አሜሪካ ካናዳ፣እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ግብፅ፣ፓኪስታን ፊሊፒን እና ሌሎችም የውጭ ሀገር ዜጎች ጦርነት ሳይባባስና መንገዶች ሳይዘጋጉ መንግስቶቻቸው እንደ እንቁላል ተንከባክበው ከጦርነቱ ሀገር ከመን አስወጥተዋል፡፡
እኛ ግን እንዳለን አለን ከኤምባሲያችን አሳዛኝ ድርጊት ጋር ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ባለፈው ሳምንት ሰኞ ነው እረፋድ 4፡00 ላይ ወንድ፣ ሴቱ፣ ወጣት፣ አዛውንቱ ፣ ህጻናትን የያዙ … ብዙ ኢትጵያውያን የመን የሚገኘው ኤምባሲ በር ላይ ተኮልኩለው ቆመዋል ሁሉም ለአንድ ነገር፡፡ በጦርነት የምትታመሰውንና ብዙ ወገኖችን እየፈጀ ካለው እሳት አውጥተው ወደ ሀገራቸው እንዲመልሷቸው በማለት በአንድ ድምፅ መቼ ነው የምትወስዱን ብሎ ለመየቅ፡፡ ምክንያቱም ተመዝግበው በመቆየታቸውና የኢምባሲው ምላሽ በመዘግየቱ ሁኔታውን ለማወቅ በቦታው ተገኘኝተዋል፡፡ የጦርነቱን አሳሳቢነት እየከፋ በመምጣቱ፡፡
በዛው ሰአት ከተማዋን ከዳር ዳር ያንቀጠቀጠ አንዲት ኢትዮጵያዊትን ጨምሮ ለብዙ ዜጎች ሞት ምክንያት የሆነ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳትን በብዙዎች ያስከተለ፣ ብዙ የሀብት ንብረትን ውድመትን ያደረሰ ከባድ ፍንዳታ የየመንን ምድር አንቀጠቀጠው፡፡ ሁሉም ባለበት ወደ መሬት ድፍት አለ፡፡ በዛው ፍጥነት የኤባሲው በርም ክርችም ተደረገ፡፡ ግራ የሚያጋባ ሆና ለዜጋው በዛን ሰአት በሩ በሰፊው ተከፍቶ ኑ ወገኖቼ ያለው ነገር እስኪበርድ ከባንዲራችሁ ስር ተጠለሉ ማለት ሲገባው የራሱን ነፍስ ለማዳን ወገንን ከእሳት ጥሎ በር በከርቸም ምን የሚሉት ጉድ ነው ፡፡ ሰው ከባንዲራው ሌላ ወዴት ይጠለላል? ይህ ነው ለወገኖቹ የቆመ ምርጥ ኤምባሲ ማለት፡፡
ታድያ አልኩኝ ሰሞኑን በፌስ ቡክና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በየመን ፣በሊብያ፣ በደቡብ አፍሪካ ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን ማንኛውንም እርዳታ ብትፈልጉ ተብሎ ብዙ የስልክ ቁጥሮች የተደረደሩት ምን አይነት እርዳታ ስንፈልግ ይሆን እንድንደውልላቸው ያስቀመጡት? በራቸው ላይ ቆመን የችግር ሰለባ ሆነን ወድቀን እያዩን በር ከዘጉብን ያን ሁላ መአት ስልክ ቁጥር መደርደሩ ለምን ይሆን?

No comments:

Post a Comment